ከአኩስምና ከቻይና ግንብ በፊት

Written by  Daniel Kibret Friday, 06 March 2015 13:03
Rate this item
(0 votes)

ከግንባታዎች ጋር ተያይዞ እየደረሰ ያለው አደጋ አሳዛኝ እየሆነ ነው፡፡ ይኼ አደጋ በሦስት ነገሮች ምክንያት እየደረሰ ያለ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ግንባታዎች ሲከናወኑ ተገቢ የሆነው ቅድመ፣ጊዜና ድኅረ ግንባታ ጥንቃቄ ስለማይወሰድ ነው፡፡ ታላላቅ ክሬኖች አገር ደርምሶ የሚሄድ ቋጥኝ አንጠልጥለው እየታዩ፣ በሥራቸው ሰውና መኪና እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ ለግንባታ ሠራተኞች በቂ የሆነ የአደጋ መከላከያ ሥልጠናና መሣሪያ አይሰጣቸውም፡፡ አማራጭ መንገዶችና የእንቅስቃሴ ቦታዎች ቀድመው ስለማይዘጋጁ ግንባታና ኑሮ ጎን ለጎን ይካሄዳል፡፡ መታጠር ያለባቸው ሳይታጠሩ፣ መሸፈን ያለባቸው ሳይሸፈኑ፣ መከደን ያለባቸው ጉድጓዶች ሳይከደኑ፣ ምልክት መደረግ ያለባቸው ቦታዎች ላይ ሳይደረጉ ግንባታዎች ይከናወናሉ፡፡ በዚህም የተነሣ በተገቢ ጥንቃቄ ሊተርፉ ይችሉ የነበሩ ሕይወቶች ይቀጠፋሉ፣ አካል ይጎድላል፣ ንብረት ይወድማል፡፡

 

ግንባታዎች በመንደሮች መካከል ሲከናወኑ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ሕጻናት የሌሉበት መንደር ይመስላል፡፡ በየቦታው ጉድጓዱ አፉን ከፍቶ ማየት የተሳናቸውን ሊውጥ አሰፍስፏል፤ አረጋውያንን ‹እስኪ ትዘልና› ይላል፡፡ ሕጻናትን ዋኝተው እንዲያልፉበት ይጋብዛል፡፡ በዊልቼር ለሚጓዙ፣ በከዘራ ለሚራመዱ፣ በክራንች ለሚታገዙ ቦታ የለውም፡፡

 

አንድ ግንባታ ከመከናወኑ በፊት የሚገነባው አካል በሚያስገባው የጨረታ ሰነድ ውስጥ የቅድመ ጥንቃቄ አሠራሮቹ አብረው እንዲገቡ ይደረጋሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ለጨረታ ሰነድ ማሟያነት ይውላሉ እንጂ ተከታትሎ የሚያስፈጽማቸው አያገኙም፡፡ በእነዚህ የጨረታ ሰነዶች ላይ ለግንባታ ሠራተኞችና ለነዋሪዎች ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ይገለጣሉ፡፡ ነገር ግን የሚቀሩት መደርደሪያ ላይ ነው፡፡ አንድን የግንባታ አካባቢ ገንቢው ሲረከብ የርክክብ ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ከዚያ በኋላ አካባቢው የገንቢው አካባቢ ነው፤ በዚያ አካባቢ ለሚደርሰው ጉዳትም ተጠያቂው እርሱ ነው፡፡ ኢንሹራንስ እንዲገባ የሚደረገውም ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን አስፈጻሚው አካል ተከታትሎ ለማስፈጸምና በሕጉ እንዲመራ ለማድረግ የዐቅምም የሙስናም ችግር ያለ ይመስላል፡፡

 

አንድ ግንባታ ሲከናወን የአደጋ መከላከያ ወጭ ከግምት መግባት አለበት፡፡ በአንድ በኩል ከግንባታው ጋር ቀጥታ ስለማይያያዝ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ወጭው ከፍተኛ ስለሚሆን ተጫራቾች የአደጋ መከላከያ ወጭን ይተውታል፡፡ ተቆጣጣሪዎችም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ያልፉታል፡፡ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሲሆኑ ደግሞ እንደ ወጭ መቀነሻ አማራጭ ይወሰዳሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ጆሮ ጭው የሚያደርግ አደጋ በየቀኑ መስማት የየዕለት ሰበር ዜናችን ሆኗል፡፡ ለዜጎች የሚገነባ ግንባታ ዜጎችን ያለ ፍላጎታቸው ይቀጥፋል፡፡

 

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ያሉን ነባር መንገዶችና ሕንጻዎች ያረጁ፣ በሚገባ ያልተገነቡና አሁን የሚደረጉ ግንባታዎች ለሚያስከትሉት ጫና ቀድመው ያልተዘጋጁ መሆናቸው ነው፡፡ በጣልያን ዘመን በተሠሩ ቤቶች ጎን፣ የጥገና ጊዜያቸውን ጠብቀው በማይጠገኑ ሕንጻዎች አጠገብ፣ እንደነገሩ ሲጠጋገን በኖረ ድልድይ ዳር፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ተጠርገውና ተስተካክለው በማያውቁበት ከተማ ውስጥ ነው ግንባታዎች እየተከናወኑ የሚገኙት፡፡ መሬት አርዕድ አንቀጥቅጥ ማሽኖች፣ አስገምጋሚ ዶዘሮች፣ ሕንጻ ነቅንቅ ቁፋሮዎች፣ ጆሮ በጥስ የመሣሪያ ጩኸቶች፣ ግድግዳ ሰንጥቅ የድንጋይ ናዳዎች ናቸው በየአካባቢዎቻችን እየተከናወኑ ያሉት፡፡ ቤቶቻችንና ሕንጻዎቻችን፣ መንገዶቻችንና ድልድዮቻችን ለእነዚህ አዳዲስ ክስተቶች ታስበው የተዘጋጁ አይደሉም፡፡ መዓት ነው የወረደባቸው፡፡ አርማጌዶን የደረሰ እስኪመስል ድረስ አካባቢያችን ይደረመሳል፣ ይገመሳል፣ ይንቀጠቀጣል፣ በየቀኑ ይለዋወጣል፡፡ የኛ ሠፈር ግን ለዚህ አልተዘጋጀችም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተደረጉ ተደጋጋሚ ጥናቶች አብዛኞቹ ነባር ቤቶች ከደረጃ በታች የሆኑ ወይም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡ ይህ እየታወቀ ግን ግንባታዎች ሲከናወኑ ሊደረመስ የሚችል ቤት፣ ሕንጻ ወይም ግንብ፣ ሊናድ የሚችል ገደል፣ ሊወድቅ የሚችል ድልድይ፣ ሊሰምጥ የሚችል ጉድባ፣ ሊሰነጠቅ የሚችል ግድግዳ መኖር አለመኖሩ ተለይቶ ጥንቃቄ ሲደረግ አይታይም፡፡ አንድ ‹ዳምጠው› መኪና ሲያልፍ ቤቶቻችን ጎንደርኛ እየጨፈሩ ያጅቡታል፡፡ ቆይተውም በዘፈኑ ብዛት ልባቸው ጠፍቶ በዚያው ይወድቃሉ፡፡

 

ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ የማሳወቅ ግዴታችንን ስለማንወጣ ነው፡፡ መንደር ለውጥ፣ ምድር አንቀጥቅጥ ግንባታ ሲከናወን ኅብረተሰቡ(በተለይም በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከተው የአካባቢው ነዋሪ) በበቂ ሁኔታ እንዲያውቀውና የራሱን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኃላፊነቱን የሚወጣ አካል ያለ አይመስልም፡፡ በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ከመስጠት ያለፈ ግዴታ እንዳለም ተዘንግቷል፡፡ በሌላው ዓለም አካባቢን የሚለውጥ ግንባታ ሲደረግ የሠፈሩ ሰው ዝርዝር ጉዳዩ ተጽፎ በየቤቱ ይሰጠዋል፡፡ ተሰብስቦም እንዲወያይ ይደረጋል፡፡ ሐሳቡን ያቀርባል፡፡ ግንባታው ለነዋሪውም ሆነ ለገንቢው ችግር በማይፈጥር መንገድ እንዲከናወን የጋራ መግባባት ላይ እንዲደረስ ይሞከራል፡፡ ማኅበረሰቡ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ይነገሩታል፡፡ ተቃውሞ ካለውም በምክንያት እንዲያስረዳ ይደረጋል፡፡ አሳማኝ ከሆነም ፕሮጀክቱ ይስተካከላል፡፡ እንዲያም ሲል ይቀራል፤ ፕሮጀክቱ የሚሠራው ለእርሱ ነዋ፡፡ በዚህ የተነሣም ዕድገት እሴት(asset) እንጂ ዕዳ(liability) አይሆንበትም፡፡

 

ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድሬዳዋ ከተማ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በተወያዩ ጊዜ የአካባቢው ሽማግሌዎች ያቀረቡት ጥያቄ እዚህ ላይ ሊጠቀስ ግድ ይላል፡፡ ከባቡሩ መንገድ ጎን ለእግረኛ የተሠራው ድልድይ ክፍት ድልድይ አይደለም፡፡ ከላይ ጣራ መሰል ነገር አለው፡፡ ነገር ግን ይኼ ድልድይ ሲሠራ ግመሎችን እንዲያሳልፍ ሆኖ አልተሠራም፡፡ ለምን? አሉ ሽማግሌዎቹ፡፡ በወቅቱ ሌላ ምላሽ ቢሰጣቸውም ምክንያቱ ግን እነርሱን ያላሳተፈና ሐሳብ ያልሰጡበት ግንባታ መከናወኑ ነው፡፡ አያውቁም ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ ያነሡት ሐሳብ ግን ሕዝብን የማያሳትፍና ይሁንታ ያልሰጠበት ሥራ ሁሉ ከሪፖርት ያለፈ ዋጋ እንደሌለው ያሳየ ነው፡፡ ድልድዩ ችግራቸውን ከመፍታት ይልቅ ራሱ ችግር ነው የሆነባቸው፡፡

 

መኖሪያ ማለት ጣራና ግድግዳ ብቻ አይደለም፡፡ አካባቢም ጭምር ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት የኖረበት ወይም እኖርበታለሁ ብሎ የሚያስበው አካባቢ በአንድ ማለዳ ተለውጦ ሲጠብቀው፣ ለነዋሪው ሕመም እንጂ ደስታ አይፈጥርለትም፡፡ አስቀድሞ የማወቅ፣ ለሚመጣው ለውጥ የመዘጋጀት፣ ለውጡ ለሚያስከትለው አሉታዊ ነገር ጥንቃቄ የማድረግ፣ ለውጡን በሚችለው ሁሉ የማገዝና ለውጡም ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ከሆነ እስከማስቀረት የሚደርስ መብት ሊኖረው ይገባል፡፡ አንድ ነገር ‹መልካም ነው› ማለትና ‹ተቀባይነት አለው› ማለት ይለያያሉ፡፡ መልካም ነገሮች መልካም ሆነው እንዳይቀጥሉ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ የሕዝብ ተቀባይነት ማጣት ነው፡፡ የመንግሥት አንዱ ኃላፊነት መልካም ነው ብሎ ያመጣው ነገር ሕዝባዊ ተቀባይነት እንዲኖረው የመሥራት ግዴታ ነው፡፡ የማስረዳት፣ የማሳወቅና የሕዝቡን ሐሳብ የመቀበል ግዴታ፡፡

 

ግንባታዎች በሚከናወኑበት አካባቢ መረጃ ሰጭ ምልክቶች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ምን እየተከናወነ ነው? ለተዘጋው መንገድ አማራጩ ምንድን ነው? መኪኖች በየት ይታጠፉ? እግረኞችስ በየት ይለፉ? ምን ጥንቃቄ ይደረግ? የሚገነባው ግንባታ አካባቢውን እንዴት ይቀይረዋል? ከፍታው፣ ጥልቀቱ፣ ስፋቱ ምን ያህል ነው? ገደል ነው ሜዳ? ውኃማ ነው ደረቅ? ዋሻ ነው ግልጥ? ከላይ የሚወድቅ ነገር አለ ወይስ የለም? በአካባቢው መኪና ማቆም ይቻላል አይቻልም? ከስንት ሰዓት እስከ ስንት ሰዓት ግንባታው ይከናወናል? ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ነው፡፡ ‹‹ምን አስቸኮላችሁ፤ እዚያው ሲደርስባችሁ ታውቁታላችሁ›› የተባለ ይመስላል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ አደጋ የሚያስከትሉ ነገሮችን እንኳን የሚያመለክት ምልክት በሚገባ አይኖርም፡፡ በዚህ ምክንያት ገደል የሚገቡ መኪኖችንና ሰዎችን እያየን ነው፡፡

 

በሰሞኑ እንኳን ከግንባታ ጋር የተያያዙ አሰቃቂ ዜናዎችን እየሰማን ያለነው እነዚህ ሦስት ነገሮች ስለተዘነጉ ይመስለኛል፡፡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስቀድሞ የሚነግራቸው በማጣታቸው የትምህርት ቤት አጥር ሥር ተቀምጠው የነበሩ ተማሪዎች በመንገድ ግንባታ ንዝረት ግንቡ ተደርምሶ መዓት ወረደባቸው፡፡ ሰኞ ዕለት ደግሞ አፍንጮ በር አካባቢ በአሮጌ ማዕድ ቤት ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ አዳጊ ልጆች በአካባቢያቸው እየተካሄደ ያለው ነገር ምን እንደሚያስከትል ስላልተነገራቸው አንዷ ለሞት አንዷም ለጉዳት ተዳረጉ፡፡ ለምን? አሁን እየገነባን ያለነው ግንባታኮ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ግንባታ አይደለም፡፡ ከአኩስም ዘመን ተነሥተን እንኳን ብናሰላ ከሁለት ሺ ዘመን በላይ በግንባታ ላይ አሳልፈናል፡፡ እንዴት እንደ አዲስ ገንቢ ስሕተቱ የግንባታውን ያህል ይሆናል? በዓለም ላይ እኛ የመጀመሪያዎቹ ገንቢዎች አይደለንም፡፡ ከቀደሙት ልንማራቸው፤ ተምረንም ልንተገብራቸው የሚገቡ ነገሮች ሞልተው ተርፈው እንዴት በ21ኛው መክዘ የ1ኛው (ቅልክ) ስሕተት ይሠራል?

 

እንደ እኔ የሚመለከታቸው አካላት እነዚህን ነገሮች ቢያደርጉ አደጋውን መቀነስ፣ ከዚያም አልፎ ማስቀረት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

 

1.  የሚቻለው ቅድመ፣ ጊዜና ድኅረ ግንባታ ጥንቃቄዎችን ማድረግ፡፡ ወጭ ለመቆጠብ ወይም ደግሞ ጉዳዩን ለማፋጠን ሲባል የጥንቃቄ ነገሮችን መዝለልና መቀነስ ቀርቶ፣ ልማዳዊ በሆነው መንገድ መሥራት አብቅቶ፣ አደጋው ቀድሞ ከመከላከል ይልቅ ለአደጋው ዜና አዘጋገብ መጨነቅ ተወግዶ የሚቻለው ጥንቃቄ ሁሉ መደረግ አለበት፡፡ ‹ማስተዋል ይጋርድሃል፣ ጥንቃቄም ይጠብቅሃል› እንዲል መጽሐፉ፡፡

 

2.  የአካባቢው ነዋሪና ተጠቃሚ ስለ ግንባታው እንዲያውቅ፣ ዐውቆም እንዲዘጋጅ፣ ሐሳብም እንዲሰጥ በዝርዝር ማወያየት፣ መረጃውን በየቤቱ መስጠት፤ ሐሳቡን መቀበልና ተግባቦትን መፍጠር

 

3.  በቂና ግልጽ ምልክቶችን በአካባቢው መጠቀም፡፡ ዝርዝር መረጃ የሚሰጡና አደጋዎችን የሚያመላክቱ ምልክቶችን በአካባቢው ሕዝብ ሊመለከት በሚችልበት ቦታ ማስቀመጥ

 

4.  ማኅበረሰቡ ጉዳዩን እንዲከታተል ማኅበረሰብ ዐቀፍ ኮሚቴ ማቋቋምና ችግሮች ከመድረሳቸው በፊት ከነዋሪውና ከሚመለከታቸው ጋር እንዲሠራ ማድረግ

 

5.  ግንባታዎቹ እየተከናወኑ ያሉት በሕዝብ መካከል ነውና የሕዝቡን እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ከዲዛይኑ ጀምሮ መሥራት፡፡ ከተማዋን በባቡር ምክንያት በአራት ክፍለ ከተማ ከፍለን ያንንም በአጥር ከልለን፣ ዘላችሁ አታቋርጡ ማለት በጆሮ ግንድ በኩል አዙራችሁ ጉረሱ እንደማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ከመነሻው ምን ያህል ተጉዞ ነው መንገድ ማግኘት ያለበት?የሚለው ነገር የታወቀ ዓለም ዐቀፍ ደረጃ አለው፡፡ ሰው በጠባዩ አጭር መንገድ ይፈልጋል፡፡ ይህንን የሰው ጠባይ በአጥር ብቻ ለማስቀረት ከመታገል ከዲዛይኑ ጀምሮ ዓለም ዐቀፍ ደረጃዎችን ተጠቅሞ ማሰቡ አደጋዎችን ያስቀራቸዋል፡፡

 

6.  ብዙ ጊዜ ዓመታት በዓላቸውን ሲያከብሩ ወይም ጠቅላላ ጉባኤ ሲያደርጉ ብቻ በመገናኛ ብዙኃን ስማቸውን የምንሰማቸው የሞያ ማኅበራት(የአርክቴክቶች፣ የሲቪል መሐንዲሶች፣ የሕንጻ ተቋራጮች፣ ወዘተ) ተገቢው ቦታና ሥልጣን ተሰጥቷቸው የግንባታዎችን ሂደት እንዲከታተሉ፣ የንሥር ተመልካችነት(watch dog)  ኃላፊነትን እንዲወጡ ቢደረግ፤

 

እንዴው በአጠቃላይ ግን የግንባታ ሂደታችንን እኛም ከአክሱም በፊት የምንገነባው፣ ቻይኖችም ከቻይና ግንብ በፊት የሚሠሩት ባንመስል መልካም ይመስለኛል፡፡ ቅንዥላቶቻችን በዐጸደ ነፍስ ሆነው ይገረሙብናል፤ ‹አሁን እነዚህ የኛ ልጆች ናቸው?› ይሉናልና፡፡

Last modified on Friday, 17 April 2015 06:52
You are here: Home Our Blog ከአኩስምና ከቻይና ግንብ በፊት