የመንገዱ ንጉስ (King of the road)

Written by  Wednesday, 01 April 2015 02:58
Rate this item
(0 votes)
የመንገዱ ንጉስ (King of the road)

 

የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ፣ ሲሮጡ የታጠቁትም የሚባል ብሂል አለን፡፡ ይህ ምን ለማለት ነው በፍጥነት፣ በለብለብ፣ ወይም በግዴለሽነት ወይም በስንፍና ገረፍ ገረፍ አድርገን የተውነው ኋላ ችግሩ ያፈጥና ዳግም  እንደምንመጣበት ሲያመላክት ይመስለኛል፡፡

የፅሁፍ አነሳሴ ተረት ለመተረት ሳይሆን በመንገድ ላይ መኪና ይዘው የሚጓዙት ሹፌሮቻችን ስነ ምግባርና የሙያ ብቃት አlዋጥልህ ስላለኝ ነው፡፡

ክላክስ ( ጡርምባ) መጠቀም በአግባቡ ሲሆን አሳልፈኝ፣ እየመጣሁ ነው ፡ ነቃ በል፣ ኧረ እያየህ፣ የሚሉና እንደ ቦታውና አጋጣሚው ደግሞ ሌላም መልእክት ይኖረዋል፡፡ ግን በቆመና ሰው ባየ ቁጥር እጁና ክላክሱ የማይለያዩትን አደንቋሪ ምን ዓይነት አሠልጣኝ ነው ለዚህ ያበቃው ያሰኛል፡፡ የሚከታተለው የለ ሆኖ እንጂ ከቅጣት ጀምሮ መንዳት እስከ መከልከል የሚያደርስ መሆኑን ግን አሠልጣኙ አልነገረውም ወይም አላስተማረውም ማለት ነው፡፡

 

አንድ ሰው ብቃት እንዳለው ተረጋግጦ መንዳት የሚያስችል ፍቃድ ሲሠጠው ብዙ ኃላፊነቶችንም አንዲሸከም አብሮ አስገዳጅ ህጎች ይሠጡታል፡፡ እነዚህም መንገዱን በጋራ አብሮ ለመጠቀም፣ የትራፊክ ህግን አክብሮ ሲነዳ፣ ከቁጥጥር ውጭ ካልሆኑ በቀር ምንም ዓይነት አደጋ ላያደርስ፣ ኢንሹራንስ ከሌለው መኪናውን ላይነዳ (ይህ ለሌላው ኃላፊነት መውሰድን ወይም ማሰብን ይመለክታል፡፡ ኢንሹራንስ የሌለው አሽከርካሪ ለራሱም ህይወት ሆነ ለሌላው ግድ እንደሌለው ያመለክታል፡፡ የራሱን ህይወት የጠላ ሰው እንዴት የሌላውን ህይወት ተንከባቦ እንዲያደርስ ኃላፊነት ይሰጠዋል)፣ ጠጥቶ ላይነዳ፣ መንገዱን ከመኪናው በሚወጣ ፈሳሽ ላያቆሽሽ፣ ካቆሸሸም ሊያፀዳ፣ ፀያፍ ነገር ላይፈጽም፣ አደንዛዥ እጾችን ላያዘዋውር እርሱም ላይጠቀም (ጫት አንዱ ነው) የመኪናውን ጤንነት  አሟልቶ መገኘት፣ (ብዙ ጊዜ ፍሬን ተበጠሰብኝ የሚል አሳፋሪ ታሪክ  አለን፡፡

 

የፍሬን አካሎች ከተስተካከሉለት እንዴት ነው ፍሬን መበጠስ ማለት፡፡ የመኪናውን እግር ሁኔታ የሚያውቀውና ችግሩን ጠንቅቆ የሚረዳ አሸከርካሪ ዛሬ ተነስቶ ተበጠሰብኝ ቢል ምክንያት አይሆንም፡፡ ይልቁንም በፍፁም ፍፁም ኃላፊነት የማይሰማውና እራሱንም ለማጥፋት ሆን ብሎ እንደሚጓዝ ሰው የሚቆጠር ነው፡፡ ምክንያቱም የፍሬን ችግር ዛሬ በዛሬ የሚከሰት አይደለምና፡፡ አንዳንዴ ኢንሹራንሶች ከለላ የሚያደርጉላቸውን ተሸከርካሪዎች ብቃት በድንገተኛ ፍተሻ ጭምር ማረጋገጥ አለባቸው እላለሁ ።ችግሩ ወደ እነርሱ ከመሄዱ በፊት፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ የስነምግባርና የኃላፊነት ዓይነቶችን መጥቀስ እንችላለን፡፡

 

 

ቅድሚያ ለእግረኛ የሚል በህግ የተደነገገ አንቀጽ አለ፡፡ ስንቶቻችን ነን ይህን በስራ ላይ የምናውለው? አንድ እግረኛ አስፋልት መሻገሪያ ላይ(ዚብራ) ካለ 30 ሜትር ርቀት መኪናችንን ማቆም እንዳለብን ስንቶቻችን እንረዳዋለን፡፡

እግረኛ በሚበዛበት፡ በትምህርት ቤት፣ ልጆች በሚጫወቱበት አካበቢ ከ30 ኪ.ሜ ፍጥነት በሰዓት በላይ መንዳት እንደሌለብንስ? "እንደንጉሱ አጎንብሱ" ሆነና እንደ ሃገሩ እንደአካባቢው አንደ አመሉ እየተባለ ህገወጡ ክፍል ህጋዊውን ሲጫነው ያም ሁኔታዎች ሲያስገድዱት ህገወጥነቱን እየተለማመደው ህጋዊ አስመሰለው፡፡

 

እስቲ ስለ ሾፌሮቻችን የሞያ ብቃት ትንሽ እናውራ፣ በተለይ ሲኖ ትራክ የሚባለውን ጊዜ ያመጣውን መኪና ሰለሚነዱት፡፡

ራሳቸውን ‘king of the road’ ብለው የሚጠሩት እኒህ ወገኖች ሥልጠናውን የሠጣቸው አካል ስነምግባሩንም አላስተማራቸውም ይሆን?፡፡

ከራሴ ልጀምር አንድ ጊዜ መኪና ይዤ አንድ ጊዜ ደግሞ በእግር እየተጓዝኩ የቀን ጉዳይ ሆኖ እንጂ ወጥተውብኝ ጨርሰውኝ ነበር፡፡ ልጄንም ይሄው ዕጣ ደርሶበታል፡፡ እርሱ ግን ቦይ ውስጥ ዘሎ በመግባት የመጋጋጥ የመቁሠል አደጋ ደርሶበታል። ይሄ እንግዲህ የሚያስከትለውን የስነ ልቦና ችግር ትታችሁ ነው፡፡ ለምን እንዲህ ታበራላችሁ(ትነዳላችሁ)፣ ሰውስ ቢጎዳ ምን ትጠቀማላችሁ ሲባሉ እኛ ለመንገዱ ልማት፣ ለባቡሩ ልማት ለእንትኑ ልማት መፍጠን አለብን፣ ሌላም ውሃ የማያነሳ ምክንያት ይደረድራሉ፡፡

 

በመሠረቱ ሀገሩ ስትገነባ የሚጠላ ፡ በጭቃ ከመሄድ በአስፋልት መሄድ፣ ከአውቶቡስ ግፊያ በባቡር መንፏለል የሚጠላ ያለ አይመስለኝም። ለልማቱ ሁሉም በግልም በተዘዋዋሪም አስተዋጽኦ ያደረጋል፡፡ አድርጓልም፡፡ ማድረግም ግድ ይላል፡፡

እናንተ የልማቱ አውራ ናችሁና የመንገድ ትራንስፖርት ህጉን እየጣሳችሁ ንዱ አልተባሉም፡፡ ወይም የትራፊክ ህግ እናንተን አይመለከትም የሚል ቀጭን ትእዛዝ አልተሰጣቸውም ከየት የመጣ ሥነ ምግባር ነው ወገንን እየገደሉና እያቆሰሉ በልማት ስም ሩጫ?

በመንገድ ላይ አንድ ሲኖ ትራክ ሲታይ አብዛኛው መኪና ሰለሚሸሽ እርስ በርሱም የመላተም አደጋ ያጋጥማል፡፡

መንገዱን በጥሩንባ ጩኸት ይሞሉትና እውነትም የመንገዱ ንጉስ ሆነው ይታዩበታል፡፡ በእነርሱ አስተሳሰብ የሰው ቀልብ መስለብ፣ አደጋ ማድረስ፣ ማቁሰልና ንብረት ማውደም የልማት አንዱ አካል ይመስላቸው ይሆን?

የመንዳት ትምህርት ሥልጠና የሚሰጡ ወገኖች ብዙውን ጊዜ አደጋ የሚያጋጥመው ከአሽከርካሪው የስነ ምግባር ጉድለት እንደሆነ ጠንቅቀው ስለሚረዱ ለዚህ ሠፊ ትኩረት ይሰጡታል፡፡

 

ለምሣሌ ሰከን ወይም ዝግ ማለት በፍጥነት ምክንያት ከሚመጣ አደጋ ይከላከላል፡፡ በተለይ የሰከነ አእምሮ ለሁሉም መልካም ነው፡፡ በህይወቴ ለሀገሬ ለወገኔ አንድ አስተዋጽኦ አደርጋለው የሚል ሰው ወገኑን አይበድልም፣ ብሎም ለአካል ጉዳትና ለውድመት አይዳርግም፡፡

ሥነ ምግባር ካለ፣ ህዝብን ማክበር ወገንን መንከባከብ ይኖራል ይህ ደግሞ በምላሹ  ለእነርሱ አክብሮትን እንክብካቤን ያስገኝላቸዋል፡፡

መንገድን በጋራ መጠቀም የሚቻለው የራስ መውደድ ጠባይ ከልተጠናወተው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ራሱን ዝቅ ያደረገ ከጎኑ ደግሞ ከፍ የሚያደረገው ይኖራል፡፡ በመተዛዘን በመተሣሠብ መጠቀም መልካም ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ይህን ሥነ ምግባር መንዳት የሚያስተምሩ ወገኖች ዘንግተውት ይሆን?

 

‹‹የመንገዱ ንጉሶች›› የስነ ምግባር ችግር ብቻ አይደለም የአነዳድ ብቃታቸውንም እጠራጠራለሁ፡፡ ለምሣሌ 50 ኪ/ሜ በሠዓት በሚነዳበት ህዝብ በበዛበት አካባቢ ከ80 በላይ ፍጥነት መንዳት ያውም በመንደር ውስጥ እንዴት መኪናውን ሊቆጣጠሩትና ሊያቆሙ እንደሚችሉ አይገባኝም፡፡

እንደዚያ እያበረሩ በመሃከል ሰው ቢገባ መኪናውን ሊቆጣጠሩና ሊያድኑ እንደማይችሉ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ ፍጥነት እንኳን ሰው ሊያድኑ ራሳቸውንም ሆነ ንብረቱን አያድኑም፡፡ ይሁን ግድ የለም ችሎታ አለን ተማምነን ነው ሊሉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በመኖሪያ አካባቢ በትምርት ቤት ህጻናት በሚጫወቱበት ከ30 ኪ/ሜ በላይ ማሽከርከር በፍፁም አይችሉም፡፡ ይህ የተራፊክ ህግ ነው፡፡ የሀገራችን የትፊክ ህግ ከሌላው ዓለም ምንም አይለየውም፡፡

 

ለአሽከርካሪዎች ትህትና እጅግ ወሳኝና ቁልፍ ነው፡፡ ራሳቸውን ባስቆጡ፣ ደመ መራራ በሆኑ፣ ትንሽ በስጨት ባሉ ቁጥር አደጋ የማድረስ እድላቸው የሠፋ ነው፡፡

ቁጡ ሰው ነገሮችን ሁሉ በኃይልና በጉልበት ለመፈፀም ይሞክራል፡፡ ሰለዚህም የኃይልና የጉልበት ውጤት አደጋ ይሆናል፡፡ አደጋው ደግሞ እስከ ሞትም ሊዘልቅ ይችላል፡፡

 

ስለዚህ የተሽከርካሪ አሰልጣኞች <‹እቤታችን ሠላም ከሌለን፣በቂ አንቅልፍ ካልተኛን ወይም ዛሬ እኔ መኪና ለመንዳት ብቁ አይደለሁም ብዬ ካሠብኩ መንዳት የለብኝም›› እያሉ ከስነምግባር ጋር የስነ ልቦና ትምህርት ሁሉ ያስተምሩ ነበር ድሮ፡፡

‹‹በህይወቴ 30 ዓመት ስነዳ ዶሮ ገጭቼ አላውቅም›› ይሉን የነበሩትን በእድሜ የገፉ አባት ሾፌሮቻችንን መተካት ለምን አዳገተን፡ ተቃራኒ እንዴት ልናፈራ ቻልን፡፡ እንግዲህ ስለ ሹፌሮቻችን ብቃት ማነስ ጣታችንን ስንቀስር ለብቃታቸው ማረጋገጫ የሰጣቸውንም አካል ይመለከታል፡፡

መቼም ችግሩ ድብቅ አይደለም፡፡ በችግሩም የሚጠቀም የለም የሚጎዳ እንጂ፡፡ ይህን በነዚህ ወገኖች ምክንያት የሚደርሰውን አደጋና ውድመት እያዩና እየሰሙ ዝምታ መምረጡም ተገቢ አይደለም፡፡

 

እንደ ምሣሌ እነሱን አነሳን እንጂ አንዲት እህታችን መንጃ ፍቃድ ለማውጣት ትምህርቱን ወስዳ ግን ‹‹ፈጣን›› ፍቃድ አግኝታ ከሃገር ትወጣለች፡፡ በውጭም አለኝ ብላ በተኩራራችበት መንጃ ፈቃድ ለውጥ ሌላ የሃገሩ ተሠጣት፡፡ እናም መኪና ይዛ ወደ ጎዳና በወጣች በእለቱ ከባድ አደጋ አድርሳ ይሄው ዳግም ላትነሳ 7 ዓመት ሙሉ ፈቃዱ ሳይመለስላት በክርክር እየባጀች ኣለች፡፡ የአንድ ቀን መዘዝ ይሏል ይህ ነው፡፡ ወዲህም የሀገራችንን መልካም ገጽታ ያበላሻል፡፡ ምን ዓይተው እንዴት የማትችለውን ትችላለች ብለው ገምግመው ሊሰጧት ቻሉም አለ፡፡ ይህ በግልጽ ወጣ እንጂ በየቤቱ ደግሞ ስንት አሳፋሪ ታሪክ ይኖራል፡፡

 

እያልኩ ያለሁት በአግባቡ ትምህርቱ ይሰጥ ነው፡፡ አንድ ሰው በብቃት ከተማረ ያንን ተግባራዊ የማያደርግበት ምክንያት የለውም፡፡ ስለዚህ ብቁ ናቸው ብለን መንጃ ፈቃዱን ስንሠጣቸው ብዙ ነገሮችን አስተውለንና ገምግመን ይሁን፡፡ ማንም በገንዘቡ ሞትና ውድመትን መግዛት የሚፈልግ የለም፡፡ ከመሠረቱ ያልተገነባ እውቀት፣ እውቀት ሊባልም ሊሆንም አይችልም፡፡

ሹፍርና በራሱ ሣይንስ ነው፣ ጥልቅ ሙያ ነው፡፡ በውጭው ዓለም እንደምናየው አንድ አሽከርካሪ የመጀመሪያዋን የመንጃ ፈቃድ ለመውሰድ ከትምህርቱና ከፈተናው ጊዜ በተጨማሪ ለአንድ አመት በልምምድ ይቆያል፡፡ እንግዲህ ከዚያ በኋላ ነው ትክክለኛው የመንጃ ፈቃድ የሚሠጠው ለዚያውም ብቁ ከሆነ፡፡

 

በተለይ የከባድ መኪና መንጃ ፍቃድ ለማግኘት የሚፈሰው ገንዘብና ጉልበት እጅግ ብዙ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የሚደረገው ጥራትና ብቃት ያለው ሾሬር ለማፍራት ነው፡፡

የኛም ከሌላው የዓለም ክፍል የተለየ አይደለም ስለዚህ ትኩረት ብቃት ላይ ትኩረት ጥራት ላይ እናድርግ፡፡

 

ሰይፉ መኮንን

Last modified on Sunday, 05 April 2015 17:52
Seyfu Mekonen

Seyfu Mekonen is a founder and administrator of ethiosafety.com. As a founder and administrator he is responsible for free and up to date safety and security informations. He can be reached: seyfu2002@yahoo.com

You are here: Home Safety Driving safety የመንገዱ ንጉስ (King of the road)