የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ

Written by  Wednesday, 01 April 2015 23:07
Rate this item
(1 Vote)

 

የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ

 

በምኖርበት ሃገር ረዢም ጉዞ በመኪና እያደረግን ሳለ አደጋ ደርሶባቸው የሠው እርዳታ የሚሹ ተጎጆዎች እናገኛለን፡፡ ቀድሞ የደረሰው የኛ መኪና በመሆኑ ከተጎዳው መኪና ውስጥ ተጎጂዎችን ጎትቶ ከማውጣት ውጭ ሌላ ያደረግነው ነገር የለም፡፡ ከእኛ በኋላ የደረሰው የሌላ መኪና ተሳፋሪዎች ግን በተገኘው ጨርቅና እንጨት የተጎጆዎችን አካል ጠግነው፣ መተንፈስ የተሳነውን ትንፋሽ ሰጥተው፣ የተሰበረውን በመኪናው ስባሪ አካል ደግፈው አስረው፣ ሳምባው የታፈነውን ደረቱን ደብድበው ከፍተው፣ አምቡላንስና ፓሊስ ጠርተው የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ሠጥተው ጉዳተኞችን እየተንከባከቡ ጠበቁ፡፡

 እኛ እግር ያዙ ስንባል ከመያዝ እንጨትና ገመድ ከማቀራረብ ውጭ ምንም የፈየድነው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ጉዳተኞቹን በዚህ ረዳናቸው፣ ህይወታቸውን ለማትረፍ ይሄን አስተዋጽኦ አደረግን የምንለው ከቁጥር የሚገባ እርባና አልፈፀምንም፡፡

 በኋላ አንቡላንስም ፖሊስም ደርሶ የመጀመሪዎቹ ረጂዎች ለተጎጂዎቹ ያደረጉላቸውን በዝርዝር ገልፀው ከተሠናበቱ በኋላ አጋጣሚው መልካም በመሆኑ እኛና እርዳታ አድራጊዎቹ ተዋወቅን፣ የየት ሃገር ዶክተሮች ወይም ነርሶች እንደሆኑ ጠየቅናቸው እነርሱም ተራ ሰዎች እንደሆኑና ምንም አይነት የህክምና እውቀት እንደሊላቸው ገለፁልን፡፡ ነገሩ ደንቆን ‹‹ታዲያኮ ተግባራችሁ ሁሉ የአንድ ህክምና አዋቂ ነበር፡፡ አልናቸው፡፡ ‹‹አዎ እያንዳንዱ ሰው በህይወቱ የሚያጋጥመው አይታወቅምና የህክምና ባለሙያ ዘንድ መድረሻ የምትሆን ጥቂት እውቀት ቀስመን እንደምታዩት ሰው እንረዳበታለን እኛም ስንጎዳ ሌላው እንዲሁ ያደርግልናል ስለዚህ እናንተም የዚህ እርዳታ አካል መሆን አለባችሁ ብለውን ተለያየን፡፡

 ልብ ያለው ልብ ይላልና ሳልውል ሳላድር የዚህ በጎ ተግባር ተቋዳሽ ሆኜ እኔም እንደሌላው ወግ ደርሶኝ እርደታ ለመስጠት በቃሁ፡፡ አሁን የሆነ የመኪናም ይሁን፣ የእሳት፣ የመውደቅም ይሁን የመታፈን አደጋ ዘልዬ የምገባ ፈጥኖ ደራሽ ሆኛለሁ፡፡

 ጎሸ አላችሁኝ፡፡? እናንተስ?

አንድ አደጋ በሚደረስበት ወቅት ዋነኞቹ ረጅዎቹ (የህክምና ባለሙያ) እስኪመጣ ወይም ተጎጂው ህክምና ቦታው እስኪደርስ ደሙ ፈሶ እንዳያልቅ፣ ወይም መተንፈስ ሳይችል ቀርቶ እንዳይሞት ወይም የስብራቱ ስቃይ ታግሶለት እንዲቆይ ማድረግ የምንችል ስንቶቻችን እንሆን፡፡

 የእያንዳንዳችን እስትንፋስ በአምላካችን እጅ እንዳለች አምናለሁ፡፡ እያልኩ ያለሁት ቀኗ ያልተቆረጠላት ነፍስን እንዴት ተንከባክበን ከስቃይዋ እናስታግሳት ነው፡፡

 በሠይፉ ፋንታሁን ዝግጅት ላይ አንድ ወጣት የኤሌክትሪክ ገመድ ወድቆበት ሲንፈራፈር በዱላ እንኳን መትቶ የሚያላቅቀው አጥቶ እጅና እግሩን እስከመቆረጥ መድረሱ ሲሰማ በእርግጥ ስለ መጀመሪያ የህክምና እርዳታና አደጋ መከላከል በፍፁም እውቀቱ እንደሌለን ያስገነዝባል፡፡

 ልጁ በቃለ መጠይቁ ወቅት ገመዱን በእንጨት እንኳ ከላዬ የሚያወርድልኝ አጥቼ የከበበኝ ሠው ሁሉ በፍርሃት ሸሽቶኝ. . . መዳን ስችል ደፍሮ የሚያስጥለኝ አጣሁ፡፡ እያለ አጋጣሚውን ሲያወሳ ላዳመጠው ልብ ይሠብራል፡፡

 በወቅቱ ትንሽ ስለመጀመሪያ የማዳን እርዳታ እውቀቱ ያለው ሰው ቢገኝ ኖሮ ይህ ወንድማችን እጅና እግሩን ባላጣም ነበር፡፡ በወጣትነት እድሜው አካለ ስንኩል ሆኖ የሰው እጅ እያየና እየጠበቀ እንዲኖር ባልተገደደም ነበር፡፡

 ለዚህ ጊዜ ነው ሥልጡንና ዝግጁ የሆነ መሠረታዊ እውቀት የጨበጠ ዜጋ የሚያስፈልገን፡፡ በመሠረቱ እንዲህ ዓይነት መሠረታዊ እውቀት በትምህርት ቤቶችና በየመስሪያ ቤቱ በተለይም በኮንስትራክሽን መስክ የተሠማሩ በቀላሉ እንዲማሩት ቢደረግ መልካም ነበር፡፡

 ነበር፣ እያልን ያለፈውን ስህተታችንን፣ ቁስላችንን፣  ከማውሳት በዘለለ ለዛሬና ለነገ ምን አስበናል፡፡ ምንስ ወጥነናል፡፡

በክፉ ዘመን ነው አሉ ረሃብ ገብቶ ሰውየው ለምኖ ያገኘውን ዳቦ ሌላ ከሱ የባሰ የተራበ ሞጭልፎት ይሄዳል፡፡ ታዲያ ይህን ያዩ ሠዎች በቁጭት፡-  ‹‹ አዬ ዳቦውን በብብትህ አስገብተህ ድብቅ ብታደርገው ኖሮ›› ደሞ ሌላው ‹‹ እየው እንዲህ በጨርቅህ ጥቅልል አርገህ ብትይዘው ኖሮ›› ሌላውም ሌላ እያለ በቁጭት ሲያብከነክኑት

‹‹ከሆነ በኋላ ምክር መገኘቱ፣

ዳቦዬ ተበላ አበላለ ከንቱ›› ብሎ ገጠመ ይባላል፡፡

 ጥቃቅን ድጋፍና እርዳታ ወዲያው ቢደረግላቸው ከጥፋት፣ ከጉዳት ሊድኑ የሚችሉ ገጠመኞቻችን ከእውቀትና ከግንዛቤ ማነስ እንዳልነበሩ ሆነው ማየት በእውነቱ ያሳዝናል፡፤ ነበር ብለን የምናወሳቸው ብዙ ገጠመኞቻችን ከእውቀትና ከብስለት ጉድለት የመነጩ መሆናቸውን ማመን አለብን፡፡

 አንድ አደጋ ሲከሰት በኃላፊነት ስሜት ወይም በወገንተኝነት ተረባርበን የምንታደጋቸው ለዚህም ብቃቱ ያለን ምን ያህል እንሆናለን፡፡ ምን ያህል ሥልጡን ባለሙያ አለን፡፡

 30 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አንዲት የሠሜን አሜሪካ ሃገር ቢያንስ እንደው ቢያንስ 29 ሚሊዩኑ ሕዝብ በመጀመሪያ የህክምና እርዳታ አሠጣጥ ሙያ የሰለጠነ እንደሆነ ሲነገር በምንሠማበት ጀሮአችን ወደ ሃገራችን መልስነው ከ80 ሚሊዮኑ ምን ያክሉ ለዚህ ዝግጁ እንደሆነ መገመቱ ራሱ ሞኝነት እደፈፀምን ያስረዳል፡፡

 አሁንስ ምን እየተደረገ ነው በመሠረቱ እናት የተፈነከተ ልጅዋን አንጠልጠላ ወደ ሃኪም ዘንድ ከመሮጥ ይልቅ በራሷ ልተወስደው የሚገባትን የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አሠጣጥ ብትቀስም ልጅዋን ታድናለች፣ የሃኪሙንም ሥራ ታቀልለታለች፡፡ ለህክምና የምታወጣውንም ትቀንሳለች፡፡

 ይህን ቀላልና ቀልጣፋ፣ ለህይወትም አስፈላጊ የሆነውን ሙያ ለመማርም ሆነ ለማስተማር ኃላፈነቱ የማን መሆን ነበረበት፡፡ ወደ ነበር እንዳልገባ እንጂ ይህን ወሳኝና አስፈላጊም የሆነውን የህይወት ማዳን ሥራ ሁሉም የህብረተሠብ ክፍል ሊያውቀው በተገባ ነበር፡፡

 እያንዳንዱ ሠው በራሱ ተነሳሽነት ሊቀስመው ሊያውቀው የሚገባ በሆነ ነበር፡፡ ቢቻልማ በትምህርት ቤቶች ለታዳጊዎች ሊሰጥ ግድ የነበረበት ሙያ ነበር፡፡ ጎልማሶችም ሆኑ አረጋውያን የህይወታቸው አንደኛው አካል አድርገው የሚያዩት በሆነ ነበር፡፡

 እናም አሁንስ ለወደፊቱ ምን አናድርግ ማንም ይህ በጎ ተግባር ይመለከተኛል ለህይወቴ እንደ አንዱ የጽድቅ ሥራ ልይዘው ይገባል የሚል፣ እና እኔም ጉዳት ቢያገኘኝ መሠል የሙያው ተጋሪዎች ይረዱኛል ብሎ የሚያስብ ዜጋ ሁሉ ነገ ዛሬ ሳይል የዚህ ባለቤት ሊሆን ይገባዋል፡፡  

 

Seyfu Mekonen

Seyfu Mekonen is a founder and administrator of ethiosafety.com. As a founder and administrator he is responsible for free and up to date safety and security informations. He can be reached: seyfu2002@yahoo.com

You are here: Home Our Blog የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ